April 26, 2022

የዓላማና የተስፋ ግንኙነት

በአንድ የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ታራሚዎች በቂ የሆነና የተሟላ የምግብ አቅርቦት ነበራቸው፡፡ ከተወሰነ የማረሚያ ቤት ቆይታቸው በኋላ እርስ በርሳቸው ስለተላመዱ በተለያዩ ጨዋታዎች እየተደሰቱና አንዳንድ ሞያ ነክ ነገሮችንም እየሰሩ መረጋጋት ጀምረዋል፡፡

ብዙም ሳይቆዩ ግን ሁሉንም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተጫጫናቸው፡፡ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ተስፈኛ ሆነው የመቆየት አቅማቸውንም አጡ፡፡

የሆነው ነገር ይህ ነው፡፡ አንድ ቀን ጠዋት ሲነሱ በማረሚያ ቤቱ ግቢ አንድ ጥግ ላይ የተከመሩ አሸዋ የሞላባቸው ጆንያዎች ነበሩና እነዚህን ጆንያዎች ካሉበት በማንሳት ወደሌላው የማረሚያ ቤቱ ግቢ ጥግ እንዲወስዱና እንዲከምሯቸው ተነገራቸው፡፡ ሁሉም ታራሚዎች በመነሳሳት ያንን ሲያደርጉ ዋሉ፡፡ ከዚያም ወደማምሻው ላይ ጠዋት ወስደው የከመሩትን የጆንያ አሸዋ ክምር ወደ ነበረበት እንዲመልሱ ታዘዙና ይህ ስራ በየቀኑ እንደሚቀጥል ተነገራቸው፡፡

እነዚህ ታራሚች በተወካያቸው በኩል አሸዋ የሞላባቸው ጆንያዎች ወዲያና ወዲህ የሚመላለሱበት ዋና ዓላማ ምን እንደሆነ ሲጠይቁ የተሰጣቸው መልስ ምንም ዓላማ የሌለው ተግባር እንደሆነና አርፈው እንዲታዘዙ ተነገራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ስሜታቸው በጣም የወረደው፡፡

ምንም ዓላማ የሌለውን ተግባር ሲደጋግሙ መኖር ተስፋ ያስቆርጣል፡፡  ምናልባት ሁል ጊዜ ተስፋ መቁረጥ የሚጫጫነን የመኖራችንን ዓላማና ትርጉም እንዲሁም በየቀኑ የምናደርጋቸውን ነገሮች ለምን እንደምናደርጋቸው ዓላማቸውን በሚገባ ስላላወቅነው ይሆን?

መልካም  ቀን