ጾም
ከሰማዕትነት አያምልጣችሁ መጽሃፍ የተወሰደ ......... በ ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅ
ጾም መድኃኒት ናት፡፡ አወሳሰድዋን በትክክል ላላወቁ ግን ጥቅም የላትም፡፡ ይህችን መድኃኒት የሚወስድ ሰው በየስንት ሰዓቱ እንደምትወሰድ፣ በምን ያህል መጠን (Dosage) እንደምትዋጥ፣ ለምን ዓይነት በሽታ እንደምትጠቅም፣ በየትኛው ወራትና በየትኛው የአየር ኹናቴ እንደምትወሰድ፣ ከእርሷ ጋር የሚሔዱና የማይሔዱ ምግቦችን እንዲሁም ሌሎች ከእርሷ ጋር የማይስማሙ ነገሮችን ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡ እነዚህን ግምት ውስጥ አስገብተን የማንወስዳት ከኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡ አንድ በሐኪም የታዘዘልንን የደዌ ዘሥጋ መድኃኒት በትክክል ከወሰድነው ከሕመማችን እንፈወሳለን፤ የነፍሳችንን ደዌ ለመፈወስ ብለን በምንወስደው መድኃኒት ደግሞ ከዚህ የበለጠ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
ጾም ኹለመናችንን የምንለውጥባት መሣርያ ናት፡፡ ምክንያቱም የጾም መሥዋዕት ማለት ከምግብ ብቻ መከልከል አይደለምና፤ ከኃጢአት ኹሉ መከልከል እንጂ፡፡ ስለዚህ እየጾምኩ ነው እያለ ራሱን ከምግብ ብቻ የሚከለክል ሰው ቢኖር እርሱ ጾምን እያቃለለና እያጥላላ ነው፡፡ እየጾማችሁ ነውን? እንግዲያውስ መጾማችሁን በተግባር አሳዩኝ፡፡ “እንዴት አድርገን እናሳይህ?” ትሉኝ ይኾናል፡፡ እኔም እንዲህ ብዬ እመልስላችኋለሁ፡- ድኻው እርዳታችሁን ፈልጎ እንደ ኾነ ቸርነትን አድርጉለት፡፡ የጠላችሁትን ሰው ካያችሁት ፈጥናችሁ ታረቁ፡፡ ባልጀራችሁ ተሳክቶለት ስታዩት በእርሱ ላይ ቅናት አትያዙ፡፡ ቆነጃጅትን ስታዩ በዝሙት ዐይን አትመኙ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያደረጋችሁ በትክክል መጾማችሁን አሳዩኝ፡፡
በሌላ አገላለጽ እፋችሁ ብቻ ሳይኾን ዐይኖቻችሁ እግሮቻችሁ፤ እጆቻችሁና የሰውነታችሁ ሕዋሳቶች በሙሉ ይጹመው እጆቻችሁ ከመስረቅና የእናንተ ያልኾነውን ከመውሰድ ይጹሙ" እግሮቻችሁ የኃጢአት ሥራን ለመፈፀም ከመፋጠን ይጹሙ፡፡ ዐይኖቻችሁ ውጫዊ በኾነ ብት ምክንያት ከመቅበዝበዝ ይጹሙ፡፡ ጥሉላትን (የፍስክ ምግብ እየበላችሁ አይደለም አይደል? እንኪያስ በዐይኖቻችሁም ክፉ ነገርን አትብሉ የሚታዩ ነገሮች ለዐይን ምግቦች ናቸውና፥ ጆሮዎቻችሁም ይጹሙ፡፡ የጆሮ ጾም ሐሰተኛ ወሬንና ሐሜትን አለመስማት የመሳሰለ ነው፡፡ አንደበታችሁም ከከንቱ ንግግር ይጹም፡፡ ዓሣንና ሌሎች ጥሉላትን ከመብላት ተከልክለን ሳለ ነገር ግን ወንድሞቻችንን በሐሜት የምናመነዥካቸውና የምንበላቸው ከኾነ ምን ጥቅም አለው? ወንድሙን የሚያማና የሚነቅፍ ሰው እርሱ የወንድሙን አካል ያቆስላል፣ ሥጋውንም ይበላል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ይህን አስመልክቶ እጅግ የሚያስደነግጥ ንግግርን የተናገረው፡፡ እንዲህ ሲል፡- “ርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ” /ገላ.5፡15/፡፡ ስታሙ በጥርሳችሁ የወንድማችሁን ሥጋ አትነክሱም፡፡ ነፍሱን ግን ታቆስሏታላችሁ፡፡ እንዲህ በማድረጋችሁ ራሳችሁን ወንድማችሁንና ሌሎች ብዙ ሰዎችን ትጎዳላችሁ፡፡አንደበታችሁ ክፉ ነገርን ከመናገር ካልጾመ ጉዳቱ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በሐሜታችሁ እናንተን የሚሰማ ወንድማችሁን የሐሜት ተባባሪ ይኾናል፡፡ በዚህ ምክንያት እርሱንም በደለኛ ታደርጉታላችሁ፡፡ የራሱን ኃጢአት እንዳይመለከት ስላደረጋችሁት ሳያውቅ ከሐሜተኞች ጎራ ይቀላቀላል፡፡ በዚህ ሰዓት የሌሎች ወንድሞቹን ድካም እየተመለከተ እርሱ ግን በመጾሙ ትልቅ የጽድቅ ሥራን እንደፈጸመ ቈጥሮ ይኩራራል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ሊታይ የሚገባው ሌላ ትልቅ ጕዳይም አለ፡፡ ይኸውም እናንተ ወንድማችሁን ስታሙ የሚያደምጧችሁ ሰዎች የምታሙትን ወንድማችሁን በመንቀፍ ብቻ አያቆሙም፡፡ ከዚያ ይልቅ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያንንም ጭምር ይነቅፋሉ እንጂ፡፡ በተለይ ሰሚዎቹ ኢአማንያን ከኾኑ ያንን የምታሙት ሰውዬ ብቻ “አመንዝራ” ብለው አያበቁም፡፡ ከዚያ አልፈው ቤተ ክርስቲያን የአመንዝራዎች ቤት እንደ ኾነች ያስቧታል እንጂ፤ ሎቱ ስብሐት! እንዲህ ስታደርጉ የእግዚአብሔርን ስም ታሰድባላችሁ። መልካም ስናደርግ እግዚአብሔር በእኛ ምክንያት እንደሚመሰገን ኹሉ ክፉ ስናደርግም በዚያው ልክ ስሙ ይዋረዳል፤ ይሰደባልምና፡፡
ዳግመኛም ይህ እናንተ የምታሙት ወንድማችሁ በልቡ እናንተን መጥላት እንዲጀምርና የባሰ ኃጢአት እንዲሠራም ትገፋፉታላችሁ፡፡ በዚህም ምክንያት በማይመለከታችሁ ነገር እጃችሁን በመክተታችሁ በራሳችሁ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድን ታመጣላችሁ፤ ያውም በወርሐ ጾም፡፡
ከእናንተ መካከል፡- “ዋሽቼ ስለ ወንድሜ ክፉ ነገርን ካልተናገርኩ ነገር ግን እውነት የኾነውን ነገር ብናገር (የሠራው ኃጢአትም ቢኾን) ምን ነውር አለው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ግድ የላችሁም! የምታወሩት ነገር እውነት ቢኾንም እንኳ አሁንም ንግግራችሁ ከነቀፋ _ አያመልጥም፡፡ “እንዴት ኾኖ?” ብላችሁ ልትጠይቁኝ ስለምትችሉ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ ልስጣችሁና ንግግራችሁ እንዴት ብሎ ክፉ እንደ ኾነ ይገባችኋል፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ስምንት ላይ የምናገኘው አንድ ፈሪሳዊ አለ፡፡ ይህ ፈሪሳዊ ስለ ቀራጩ ወንድሙ የተናገረው ነገር እውነት ነው፡፡ እውነቱን ስለተናገረ ግን ተጠቀመ ወይስ ተጎዳ? ፍጹም አልተጠቀመም! እንዲህ በማለቱ (እንደ እናንተ አባባል እውነትን በመናገሩ ) አልተመለሰምን? በመጸለዩና በመጾሙስ ምን ጥቅም አገኘ? እስኪ አሁንም ልጠይቃችሁ እናንተም መልሱልኝ። ተራ ኃጢአተኛ አልነበረምን? ከወንጌሉ እንደምናነበው ያ ቀራጭነጢአተኛ እንደነበረ ግልጽ ነው ፈሪሳዊው ግን በጸሎቱና በጾሙ መካከል የራሱን ኃጢአት ከማዕበና ከማሳሰብ ይልቅ ወንድሙን እያማ ስለነበረ ወደ ቤቱ የተመለሰ የጾምን ዋጋ ላያ ባዶውን ነበር፡፡ ባዶ እጁን
ወንድሞቼ! “እከሌ እኮ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ኃጢአት ሠርቷል” ብላችሁ የምታሙትን ወንድማችሁ ከዚያ ኃጢአቱ ነጻ እንዲወጣ ትፈልጋላችሁን? እንግዲያውስ ስለ ኃጢአቱ አልቁስለት፤ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩለት፤ ለብቻ ወስዳችሁም ምከሩት እንጂ አትሙት፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሎ ጽፎላቸው ነበር፦ “ነገር ግን ወዳጆች! እናንተን ልናንጻችሁ ኹሉን እንናገራለን፡፡ ስመጣ እንደምወደው ሳትኾኑ አገኛችሁ ይኾናል፤ እኔም እንደምትወዱት ሳልኾን ታገኙኝ ይኾናል ብዬ እፈራለኹና፡፡ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይኾናሉ፡፡ እንደገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኤ እንዲያዋርደኝ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ” (2ኛ ቆሮ.12፡19-21)፡፡ ስለዚህ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በትልቁ ደግሞ እንደ ጌታችን “ኃጢአተኛ ነው” የምትሉትን ወንድማችሁን እዘኑለት፤ ውደዱትም፡፡ ለብቻው አድርጋችሁ ስትነግሩትም አመጣጣችሁ እርሱን ለመምከርና ለመገሠጽ ደግሞም ከኃጢአቱ እንዲመለስ እንጂ እርሱን ከመጥላታችሁ የተነሣ እንዳልኾነ አስረዱት፡፡ ስለዚህ በትክክል ከያዘው ደዌ እርኩሱን መፈወስ ስትፈልጉ ወደ እርሱ መሔድን አትፍሩ፣ ጥፋቱን ለመንገርም አትፈሩ፡ ሐኪሞችን አይታችሁ ክኾነ አንድ አስቸጋሪ ታማሚን ለማከም መጀመርያ ቀስ ብለውና ጊዜ ወስደው ታማሚዉን ያሳምኑታል፣ ከዚያም መራራውን መድኃኒት ይሰጡታል፡፡ ታካሚውም በሽታው የሚድን ክኾነ ይፈውሳል፡፡ ሐኪሙን የሚያመሰግነው ግን ሲድን ነው፡፡ እናንተም እንደዚህ ሐኪም መኾን አለባችሁ፡፡ ከምታሙት ይልቅ የወንድማችሁን ቁስል የበለጠ እንዳይመረቅዝ ፈጥናችሁ ወደ ሐኪም ቤት (ወደ ቤተ ክርስቲያን) ውሰዱት፡፡ ከዚያም ሐኪም (ካህን) እንዲያየው አድርጉ፡፡ እንዲህ ስታደርጉ እናንተም ወንድማችሁም በእጅጉ ትጠቀማላችሁ፡፡ እውነተኛ ጾም ጾማችሁ ማለትም እንዲህና ይህን የመሰለ መልካም ምግባር ስታደርጉ ነው፡፡
ሐሜተኞችን ብቻ ሳይኾን ክፉ ንግግርን የሚያደምጡትንም ጭምር ጆሮአቸውን ከዚሁ ቆሻሻ እንዲያርቁ እናገራለኹ፡፡ ከመዝሙረኛው ጋር በመኾን እንዲህ በሉ፡- “ወንድሙን በስውር የሚያማን እርሱን አሳደድሁ” (መዝ.100፡5)፡፡ ከእናንተ ጋር ወንድሙን ለማማት ብሎ የመጣ ካለ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፡- “ስለ እርሱ መልካም ነገር የምትናገርለት አሊያም ደግሞ የምታመሰግነው ወንድም ካለህ ደስ የሚያሰኝ ጨዋታህን ለማድመጥ ጆሮዬ የተከፈተ ነው፡፡ ክፉ ንግግርን የምታወራ ከኾነ ግን ይህን ቆሻሻ ወደ ጆሮዬ እጨምር ዘንድ ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡ ወንድምህ ክፉ መኾኑን ብትነግረኝ ምን ይረባኛል? ይልቁንም እንዲህ ስታደርግ ራሴን እንድጎዳና ያለኝን እንዳጣ ታደርገኛለህ፡፡ ስለዚህ ወንድሜ! ስለ ወንድማችን ጥፋት ከምናወራ ይልቅ ስለ ራሳችን ኃጢአት እንጨዋወት፡፡ የሠራናቸውን ጥፋቶች ይቅርታ እንዴት እንደምናገኝባቸው እንጨነቅ፡፡ ስለ ራሳችን ኃጢአት ብቻ ብንነጋገር እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ወንድሜ! ንገረኝ እስኪ! በዐይናችን ውስጥ ያለውን ምሰሶ ሳናጸዳ የወንድማችንን ጕድፍ በማውራታችን የሚደረግልን ምሕረት ይኖራልን? ለምንስ በእዝነ ልቡናችን ውስጥ ሌላ ኵክ እንጨምራለን? …”
ስለዚህ ይህንን አውቀን በኹለንተናችን እንጹም፡፡ ክፉ ከመናገር እንጹም፡፡ ክፉ ከመስማት እንጹም፡፡ ክፉ ከማየት እንጹም፡፡ ወደ ክፉ ከመሔድ እንጹም፡፡ ክፉ ከማድረግ እንጹም …
የዐዋጅ ጾም ሲገባ መንፈሳዊ የበጋ ወራት እንደገባ ልብ እንበል፡፡ የጦር መሣሪያችንን እንወልውል፡፡ ከእርሻቸው አዝመራውን የሚሰበሰቡት ገበሬዎች ማጭዳቸውን ይሳሉ፡፡ ነጋዴዎችም በከንቱ ገንዘባቸውን ከማባከን ይከልከሉ፡፡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባትም መንገዳቸውን ያቅኑ፡፡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምትወስደው ጎዳና ቀጭንና ጠባብ ናትና በጥንቃቄ እያስተዋልን እንጓዝ
ወንድሞቼ! በበሽታ ምክንያት ከምግብ ባለ መከልከላችን የሚወቅሰን ጤናማ ሰው የለም፡፡ ከዚሁ በላይ ደግሞ የዋህና ሰው ወዳጁ ደግሞም ከምንችለው በላይ ሸክምን የማይጭንብን አምላክ ነው ያለን፡፡ የእርሱ ፈቃድ እኛ ከምግብ እንድንከለከል፤ ወይም እንዲኹ “ሰው ምን ይለኛል?” ብለን እንድንጾም፤ ወይም ሆዳችን ባዶ ኾኖ የረሀብ ስሜት እንዲሰማን ማድረግ አይደለም፤ ከማንኛውም ክፉና ዓለማዊ ምግባር ጾመን ለትሩፋተ ሥጋ ወነፍስ እንድንተጋ ነው እንጂ፡፡ ራሳችንን በተስተካከለ ሕይወት የምንመራ፣ መብላት ያለብንን ያህል መጥነን የምንበላ፣ ፍላጎታችንን ኹሉ ወደ ሰማያዊ ምሥጢር የምንመልስና መላ ዘመናችንም መልካም ነገርን ብቻ የምናደርግ ብንኾን ኖሮ የጾምን ዋጋ ለማግኘት ብለን መጾም ባላስፈለገን ነበር፡፡ ኾኖም የሰው ልጆች ስንባል ግዴለሾችና ምቾትን የምንሻ ስለኾንን ከምድራዊ አባትም ኾነ ከምድራዊት እናት በላይ ስለ እኛ የሚጠነቀቀው ሐኪማችን (እግዚአብሔር) ይህንን ግዴለሽነታችንና አላስፈላጊ ቅምጥልነትን ፈውሰን ከዓለማዊ ምግባር ወደ መንፈሳዊ ምግባር _ እንድንገባ ጾም የተባለች መድኃኒትን አዘጋጀልን፡፡
ስለዚህ በበሽታ ምክንያት ራሳቸውን ከምግብ መከልከል ያልቻሉትን እንዲበሉ ግን ደግሞ ከክፉ ምግባር እንዲጾሙ እንመክራቸዋለን፡፡ ከምግብ በቀር በሌላው መንፈሳዊ ነገር አብልጠው እንዲተጉ እንመክራቸዋለን፡፡ በሽተኞች ከምግብ መከልከል ባይችሉም በእውነት የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ የሚያስከፍቱ ሌሎች ብዙ የድህነት መንገዶች አሉዋቸው፡፡ ስለዚህ በሕመም ምክንያት ከምግብ መከልከል ካልተቻላችሁ (ከንስሐ አባቶቻችሁ ጋር በመመካከር) አብዝታችሁ ምጽዋትን ስጡ፡፡ ከምግብ መከልከል ባትችሉ አብልጣችሁ ጸልዩ፡፡ ከምግብ መከልከል ባትችሉ ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር የተጋችሁ ኹኑ፡፡ በሽታችሁ ይህን ከማድረግ አይከለክላችሁምና… እንዲህ የምታደርጉ ከኾነ እውነተኛ ጾምን ጾማችኋል፡፡ እግዚአብሔርም ከዚህ የበለጠ ከእናንተ የሚሻው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ሐኪማችን ከጥሉላት እንድንከለከል የሚያዘን ፈቃደ ሥጋችን ደክሞ ፈቃደ ነፍሳችን እንዲበረታ በዚያም ትእዛዛቱን እንድንጠብቅ ነውና…
በአጠቃላይ በጾም ሰዓታችሁ ጊዜም ይኹን በሌላ ጊዜ ሦስት ነገሮችን በሕሊናችሁ ትይዙ ዘንድ እንመክራችኋለን፡፡ እነእርሱም ክፉ ከመናገር መከልከልን፣ ማንንም ሰው እንደጠላት ከማየት መቆጠብንና እንደልምድ አድርጋችሁ ከያዛችሁት መሐላ ትርቁ ዘንድ፡፡ በአጨዳ ላይ ያለ ገበሬ እህሉን ከማሳው በአንዴ እንደማይሰበስብ ነገር ግን በጥቂት በጥቂቱ እንደሚሰበስብ ኹሉ እኛም እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ በዚህ የጾም ወቅት ልንለማመዳቸው እና መልካም ልምዶቻችን ልናደርጋቸው ይገባናል፡፡ እንዲህ በማድረጋችንም በቀላሉ መንፈሳዊ ጥበብን ገንዘብ ማድረግ ይቻለናል፡፡ በዚህም ዓለም ሳለን መልካም ተስፋ ያለውን አዝመራ በሚመጣውም ዓለም በክርስቶስ ፊት ያለፍርሐት በደስታ እናፈራለን፡፡ ተሞልተን እንድንቆም ይረዱናል፡፡
ለዚህ የሚያበቃንን ጸጋ አግኝተን የክብሩ ወራሾች ያድርገን፡፡