ምን ፍሬ አፈራን?
በ ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅ | ከሰማዕትነት አያምልጣችሁ መጽሃፍ የተወሰደ | ትርጉም ገብረ እግዚአብሄር ኪደ
ልጆቼ! እስኪ ፍቀዱልኝና አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ትመላለሳላችሁ፡፡ መልካም ነው፡፡ ግን ምን ለውጥ አመጣችሁ? ምን ፍሬ አፈራችሁ? ታገለግላላችሁን? ታዲያ ከአገልግሎታችሁ ምን ረብሕ አገኛችሁ? ጥቅምን ካገኛችሁ በእውነት ምልልሳችሁ የብልህ ሰው ምልልስ ነበር ማለት ነው፡፡
ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ወንጌላውያን እንዲህ እያስተማሩን ሳለ የማንለወጥ ከኾነ ግን የእስከ አሁን ምልልሳችን የአይሁድ ምልልስ ነበር ማለት ነው፡፡ አይሁዳውያን ሕገ ኦሪትን የተሰጠቻቸው ኃጢአታቸውን በእርሷ መስታወትነት ዐይተው ንስሐ እንዲገቡባት ነበር፡፡ እነእርሱ ግን የንስሐ ፍሬ ሳያፈሩባት እንዲኹ ይመኩባት ነበር፡፡ ስለኾነም ለሕይወት የተሰጠቻቸውን ሕግ ሞት ኾና አገኟት፡፡ እኛም እንዲህ ለኵነኔ ያይደለ ለጽድቅ የተሰጠችን ወንጌል ፍሬ የማናፈራበት ከኾነ ከአይሁዳውያን የባለ ቅጣት ትፈርድብናለች።
እስኪ ምሳሌ መስዬ ላስረዳችሁ፡፡ አንድ የሚታገል ሰው (wrestler) በየጊዜው ተጋጣሚውን እንደ ምን ማሸነፍ እንዳለበት ልምምድ የሚያደርግ ከኾነ ክህሎቱ ይዳብራል፡፡ ተጋጣሚውንም በቀላሉ ማሸነፍ ይቻላል፡፡ በየጊዜው የሚያነብና ራሱን የሚያሻሽል (Update የሚያደርግ) ሐኪም ጐበዝ ዐዋቂና ሕመምተኞችን በአግባቡ የሚረዳ ይኾናል፡፡ በየቀኑ ቃሉ የሚነገረን እኛስ ምን ለውጥ አመጣን? ምንስ ፍሬ አፈራን?
እየተናገርኩ ያለሁት ለአንድ ዓመት ብቻ በቤተ ክርስቲያን የቆዩትን ምእመናን አይደለም፡፡ እየተናገርኩ ያለኹት ከልጅነታችን አንሥተን በቤቱ ለምንመላለስ እንጂ፡፡ ይህን ያህል ዘመን በቤቱ እየተመላለስን ፍሬ ካላፈራን ቤተ ክርስቲያን ደርሰን ብንመጣ ምን ጥቅም አለው? አባቶቻችን አብያተ ክርስቲያናት ያነጹልን ለምንድን ነው? ዝም ብለን እንድንሰባሰብ ነውን? መሰባሰቡን'ማ በገበያ ቦታም መሰባሰብ እንችላለን፡፡ _ አበው አብያተ ክርስቲያናትን ያነጹልን ቃሉን እንድንማርበት፣ በተማርነው ቃልም የንስሐ ፍሬ እንድናፈራበት፣ ሥጋ ወደሙን እንድንቀበልበት፣ እርስ በእርሳችን እንድንተራረምበት እንጂ ለሌላ ዓላማ አይደለም፡፡